Play all audios:
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ የሰላም አራማጅ ማኅበራት ተወካዮችን በቫቲካን ተቀብለው መልዕክት አስተላልፈዋል። ቅዱስነታቸው ባለፈው ዓመት በጣሊያን በተካሄደ አንድ የሰላም መድረክ ላይ ከተካፈሉ የሰላም ደጋፊ ማኅበራት ተወካዮች ጋር ተገናኝተው ተነጋግረዋል። ቅዱስነታቸው ለአባላቱ ባደረጉት ንግግር፥
“ቅዱስ ወንጌል እና የቤተ ክርስቲያን ማኅበራዊ አስተምህሮ ለክርስቲያኖች የማያቋርጥ የድጋፍ ምንጮች ናቸው” ብለው፥ ሰላምን ለመገንባት ለሚደረገው ጥረት ትክክለኛ መንገድ ጠቋሚ እንደሆኑ አስረድተዋል። የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ባለፈው ዓመት
በጣሊያን ቬሮና ከተማ ውስጥ በተዘጋጀ የሰላም መድረክ ላይ የተሳተፉ ከ300 በላይ የልዩ ልዩ ማኅበራት እና ንቅናቄ ተወካዮችን ዓርብ ግንቦት 22/2017 ዓ. ም. በቫቲካን ተቀብለው መልዕክት አስተላልፈዋል። በቫቲካን የተካሄደው ይህ ስብሰባ፥ ነፍስሔር ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የተገኙበት
የቬሮና የሰላም መድረክ ቀጣይ እና የቤተ ክርስቲያን ማኅበራዊ አስተምህሮን በማስመልከት የሚካሄዱ ልማዳዊ የውይይት መድረኮችን እና የውሳኔ ሃሳቦችን እንደገና ለማስጀመር ያለመ እንደሆነ ተገልጿል። ከተጎጂዎች ጋር መቆም ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ለማኅበራት ተወካዮች ባስተላለፉት መልዕክት፥ “ሰላምን
መገንባት የሚጀምረው ከተጎጂ ወገኖች ጎን በመቆም እና ነገሮችንም ከእነርሱ አንጻር በማየት ነው” ብለው፥ የነፍስሔር ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስን ሃሳብ ደግመዋል። “ይህ አካሄድ ልብን፣ አካሄዶችን እና አስተሳሰቦችን ለሰላም ለማዘጋጀት፣ ለሰብዓዊ ክብር ዝቅተኛ ግምት በሚሰጥ ባሕል ላይ የተመሠረተ
የጎጂ ሥርዓት ኢ-ፍትሃዊነትን ለማውገዝ አስፈላጊ ነው” ብለዋል። ከዚህም ጋር በማያያዝ፥ በጋዛ እየተካሄደ ባለው ጦርነት፥ የቤተሰብ አባላት የተገደሉባቸው የአንድ እስራኤላዊ እና የአንድ ፍልስጤማዊ የሰላም ጥማትን በመጥቀስ፥ እነዚህ ሁለቱ ዛሬ አብረው የሚሠሩ ጓደኛሞች መሆናቸውን ገልጸዋል። ወደ ሰላም
የሚወስድ መንገድ ለሰላም የተዘጋጀ ልብ እና አእምሮን እንደሚጠይቅ የገለጹት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ ለሌሎች ትኩረት የሚሰጡ እና በዛሬው አውድ ውስጥ ያለውን የጋራ ጥቅምን የሚገነዘቡ መሆን እንዳለባቸውም አስረድተዋል። በዚህ ረገድ በሠላም መድረክ ላይ የሚሳተፉ ሰዎች ቁርጠኝነት እጅግ
አስፈላጊ እንደሆነ ገልጸው፥ “ተጨባጭ የሆኑ የተግባር ውጥኖቻቸው እና ድርጊቶቻቸው ተስፋን የሚሰጡ ናቸው” ሲሉ ተናግረዋል። ወጣቶችን የሰላም ግንባታ ማስተማር ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ በዓለማችን እና በማኅበረሰባችን ውስጥ እየደረሰ ያለውን ዓመፅ በማስመልከት እንደተናገሩት፥ ወጣቶች የሕይወትን
ትርጉም ማወቅ እንዳለባቸው፥ መልካም የሆኑ ምሳሌዎችን በመከተል የእርስ በርስ ውይይት እና የመከባበር ባሕልን መለማመድ መቻል እንዳለባቸውም አሳስበዋል። “ግፍ እና ደል ቢደርስባቸውም በቀልን ወደ ጎን ትተው ሰላምን የሚመርጡ፥ ከሁከት የራቀ ሰላማዊ ዓለምን ለመገንባት ዋና ተዋናዮች ይሆናሉ” ሲሉ
አስገንዝበው፥ ብጥብጥ እና ጦርነት የሌለበት ጎዳናን መከተል የውሳኔዎቻችን፣ የግንኙነታችን እና የተግባሮቻችን መለያ ሊሆን ይገባል” ብለዋል። ቅዱስ አባታችን፥ ክርስቲያኖች ሰላምን ለማምጣት በሚያደርጉት ጥረት ቅዱስ ወንጌል እና የቤተ ክርስቲያን ማኅበራዊ አስተምህሮ የማያቋርጡ የድጋፍ ምንጮች እንደሆኑ
ገልጸው፥ ሰላምን መገንባት የሁሉ ሰው አደራ በመሆኑ ቅዱስ ወንጌል እና የቤተ ክርስቲያን ማኅበራዊ አስተምህሮ ሰላምን ለመገንባት ትክክለኛ መንገድ ጠቋሚዎች ናቸው” ሲሉ አስረድተዋል። ለሰላም የቆሙ ተቋማትን ማዘጋጀት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ ለሰላም ደጋፊ ማኅበራት ተወካዮች ያደረጉትን ንግግር
ሲያጠቃልሉ፥ “ሰላምን የምትፈልጉ ከሆነ ከፖለቲካ፣ ከትምህርት፣ ከኢኮኖሚ እና ከማኅበራዊ ተቋማትን በተጨማሪ ለሰላም የቆሙ ተቋማትንም ማቋቋም ያስፈልጋል” ብለዋል። ስለዚህ በመንፈስ ቅዱስ ጸጋ በኩል ወደ ልባችን ስለፈሰሰው የእግዚአብሔር ፍቅር ምስጋና ይግባውና፥ በታሪክ ውስጥ የአንድነት፣ የኅብረት እና
የወንድማማችነት እርሾ ሆናችሁ እንድትገኙ አበረታታችኋለሁ” በማለት ንግግራቸውን ደምድመዋል።